በጦርነት ለተጎዱ አካባቢዎች ልማት የሚውል የብድር አቅርቦት በዝቅተኛ ወለድ ሊቀርብ ነው-የገንዘብ ድጋፉ የተገኘው ከአውሮፓ ኅብረትና ከጀርመን ልማት ባንክ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በጦርነት ለተጎዱ የአፋር፣አማራና ትግራይ አካባቢዎች ለሚገኙ አነስተኛ የብድር ተቋማትና ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት የሚውል የብድር አቅርቦት በባንኮችና በማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት አማካኝነት ለማስተላለፍ በሚቻልበት ሒደት ዙሪያ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡
በውይይት መድረኩ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኢሳያስ ካሳ እንደገለጹት ከአውሮፓ ኅብረትና ከጀርመን ልማት ባንክ የተገኘውን የገንዘብ ድጋፍ በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት ታሳቢ ያደረገ ፕሮጀክት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ባንኩ ከዓለም አቀፍ ተቋማቱ ያገኘውን ገንዘብ በተመረጡ ባንኮችና የአነስተኛ አበዳሪ ተቋማት አማካኝነት በዝቅተኛ ወለድ የሚያስተላለፍ ሲሆን ከፋይናንስ አቅርቦቱ በተጨማሪም የሥልጠናና አቅም ግንባታ እንዲሁም የዲጂታል ፋይናንስ ሥራዎች የፕሮጀክቱ አካሎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ዶክተር ኢሳያስ ካሳ የወለድ ምጣኔው አነስተኛ የሆነበት ዓላማ አካባቢው በጦርነት የተጎዳ በመሆኑና ኢኮኖሚው እንዲያገግም ታሳቢ ያደረገ መርሐ ግብር በመሆኑ ባንኮችና የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትም ገንዘቡን ሲያስተላልፉ የትርፍ ሕዳጉን ብቻ ሳይሆን የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ ትኩረት መስጠት ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
በውይይቱ የተሳተፉ የዘርፉ ባለድርሻ አካላትም በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎች ገበያ ለማረጋጋትና ሴቶችና ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታሰቦ ለተነደፈው ፕሮጀክት ስኬታማነት የበኵላቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
