ኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከባንኮችና ከማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት አካሄደ

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከአፍሪካ ልማት ባንክ በተገኘ ድጋፍ ወጣቶችና ሴቶች ስራ ፈጣሪዎችን ለመደገፍ በሚቻልበት ሁኔታ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በዛሬው እለት በባንኩ ዋና መስሪያ ቤት ውይይት አካሄደ፡፡
ውይይቱ በተለይ በግብርና ዘርፍ የተሰማሩ የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ወጣቶችና ሴቶች ስራ ፈጣሪዎችን በዝቅተኛ ወለድ የብድር አቅርቦት እንዲያገኙ በማድረግ ለመደገፍ ታሳቢ ያደረገ ሲሆን በሃገሪቱ በሚገኙ የተመረጡ ባንኮች እና አነስተኛ የገንዘብ አቅራቢ ተቋማት (የማይክሮ ፋይናንስ) ጋር የተካሄደ ነው፡፡
በወጣቶችና በሴቶች ስራ ፈጣሪዎች ዘርፍ ትልቅ አሻራ ያላቸው የፋይናንስ ተቋማት እገዛቸውን ወደተሻለ ደረጃ ከፍ በማድረግ አዳዲስ ሃሳቦችን በማምጣት እያደረጉት ያለው አስተዋጽዖ የሚበረታታ መሆኑን የስራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል በውይይቱ ወቅት ተናግረዋል፡፡

በአገራችን አብዛኛው ነዋሪ በገጠር የሚገኝ በመሆኑ በገጠሩ የአገራችን ክፍል ያለውን የስራ አጥነት ችግር ለመፍታት የፋይናንስ ተቋማት ተደራሽነታቸውን በማስፋት የስራ እድል ፈጠራ ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባቸው ሚኒስትሯ አመላክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኢሳያስ ካሳ በበኩላቸው ባንኩ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የፋይናስ ድጋፍ በመስጠት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው የውይይቱ ተሳታፊ ተቋማትም በቀጣይ ለሚሰሩ ስራዎች ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ አሳስበዋል፡፡ አያይዘውም የውይይት መድረኩ መዘጋጀቱ ፕሮጀክቱን ከግብ ለማድረስ የሁሉም ተቋማት የጋራ ጥረትና ትብብር አስፈላጊ መሆኑን የሚያስጨብጥ በመሆኑ ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ልማት ባንክ በኩል በአፍሪካ ልማት ባንክ ድጋፍ ተግባራዊ ለማድረግ በታቀደው ፕሮጀክት (Agri-MSMEs Development for Jobs Project) አተገባበርና በባለድርሻ አካላት ሚና ላይ ያተኮረ ማብራሪያ የቀረበ ሲሆን ተሳታፊዎችም የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ይህን ፕሮጀክት ተግባራዊ እንዲሆን ለወሰደው ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት ምሰጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
አክለውም የፕሮጀክቱ ተግባራዊ መሆን እንደሃገርም እንደ ተቋምም የሚኖረው ፋይዳ ቀላል የሚባል ባለመሆኑ ከሚመለከተው ባለድርሻ አካል ጋር በቅርበት በመነጋገር ለውጤታማነቱ በጋራ እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኢሳያስ ለተነሱ ሃሳቦች በሰጡት ምላሽ ባንኩ ለትርፍ ሳይሆን ሀገራዊ ልማትን የሚደግፍ ተቋም እንደመሆኑ ከተቋማቱ ጋር በልዩ ክትትልና ድጋፍ በጋራ ለመስራት የበኩሉን ጥረት እያደረገ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ይህንን ፕሮጀክት መነሻ በማድረግ ወደፊት ለሚሰሩ ሰፊ ስራዎች መሰረት የሚሆኑ ሃሳቦችን የፋይናንስ ተቋማቱ በማንሳት፤ በትብብር ለመስራት ያሳዩት ተነሳሽነት የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡ 
ባንኩ ለፕሮጀክቱ ስኬታማነትና ለቀጣይ ስራዎች በባለቤትነትና በሃላፊነት የሚሰራ መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ኢሳያስ ከፖሊሲና ከአሰራር ጋር ያሉ ችግሮችን ከሚመለታቸው አካላት ጋር በጋራ በመፍታት ለስኬታማነቱ የበኩላችንን ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡
የስራና ክህሎት ሚኒስትሯ በሰጡት የማጠቃለያ ሃሳብ የውይይቱ ተሳታፊዎች ከፕሮጀክቱ ጋር ቀጥታ ተያያዥነት ያላቸው እንደመሆናቸው እስከዛሬ ከተሄደበት መንገድ በተለየ ሁኔታ ለመሄድ መሞከር እንደሚገባ ገልጸው ለፕሮጀክቱ ስኬታማነት የሙያተኞች እና የሃላፊዎች  ሃሳብና አስተያየት በሙሉ ልብ አጣምሮ መሄድ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡
ሁሉም በባለቤትነት ስሜት ፕሮጀክቱን ማሳካት በሚችልበት ሁኔታ ላይ መምከር እና መፍትሔ እያስቀመጠ መሄድ እንደሚገባ በመግለጽ የኢትዮጵያን ወጣት ወደ አንድ ምእራፍ በማሻገር ረገድ ሁሉም ተቋም የሚነገር ታሪክ ሰርቶ ማለፍ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡