የኢትዮጵያ ልማት ባንክ እና የማሽነሪ አምራቾች ማህበር የጋራ ስምምነት ተፈራረሙ
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከአገር ውስጥ ማሽነሪ እና ማሽነሪ ዕቃዎች አምራቾች ማህበር ጋር የሥራ ስምምነት አደረገ። በሚያዝያ 26 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል በተከናወነው በዚህ ስነ-ስርዓት ላይ፣ ስምምነቱ የአገር ውስጥ ምርቶችን ለማበረታታት ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
የባንኩ ምክትል ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው በላይ እንደገለጹት፣ ስምምነቱ ደንበኞች የሚፈልጓቸውን ማሽኖች በአንድ የዋጋ ማቅረቢያ (Single Quotation) በቀላሉ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። ይህም የሚሆነው የአገር ውስጥ አምራቾች መረጃ በባንኩ የመረጃ ቋት (Database) ውስጥ እንዲካተት በማድረግ ነው። በተጨማሪም ምርቶቹ እዚሁ አገር ውስጥ የሚመረቱ በመሆናቸው፣ ደንበኞች ከሽያጭ በኋላ የሚያስፈልጉ የጥገና እና የመለዋወጫ አገልግሎቶችን (After Sales Service) ያለምንም እንግልት ማግኘት እንዲችሉ ትልቅ ዕድል ይፈጥራል።
