የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ልማት ባንክን የስድስት ወራት የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ገመገመ
- February 4, 2025
- Posted by: admin
- Category: News
ቋሚ ኮሚቴው ባንኩ ለሚሰራቸው ሀገራዊ የልማት ስራዎች መረጋገጥ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጿል፡፡ይህ የተገለፀው ጥር 26፣ 2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ ልማት ባንክ ዋና መሥሪያ ለተገኘው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የባንኩ የ2024/25 በጀት የግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት በቀረበበት ወቅት ነው፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ፕሮፌሰር መሐመድ አብዶ እንዳሉት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለሀገር የልማት እንቅስቃሴ ከፍተኛ እገዛ እያደረገ ያለ ባንክ ነው፡፡ባንኩ በሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ የሚጠብቀበትን እየተወጣ እንዲቀጥል መልካም አፈፃፀም በታየባቸው በስራ እድል ፈጠራ፣የህዝቡን ኑሮ የሚያሻሽሉ ስራዎችን በስፋት እንዲሰራና አማራጭ የሀብት ምንጭ እንዲኖረው ለማድረግ ቋሚ ኮሚቴው አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ ሰብሳቢው ቃል ገብተዋል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው ከባንኩ የቀረበውን ሪፖርት ካዳመጠ በኋላ ከአባላቱ የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያይቶች ተነስተው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።የቋሚ ኮሚቴው አባላት የባንኩን የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት መነሻ በማድረግ ላነሷቸው ጥያቄዎች የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዶ/ር እመቤት መለሰን ጨምሮ የሚመለከታቸው የባንኩ ምክትል ፕሬዚዳንቶች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በዚህ ወቅት ዶ/ር እመቤት እንዳሉት ባንኩ ሀገራዊ የልማት ስራውን በተሟላ መልኩ መወጣት የሚያስችሉ የተለያዩ የአሰራር ስልቶችን መዘርጋትና የፖሊሲና የስትራቴጂ ዝግጅት ስራዎች ከፊቱ የሚጠብቁት በመሆኑ በትኩረት በመስራት ላይ መሆናቸውን ለቋሚ ኮሚቴ አባላቱ አብራርተዋል።የቋሚ ኮሚቴ አባላት በሰጡት አስተያየት የቀረበዉ ሪፖርት ጥሩ መሆኑን ገልፀዉ በተለይ በብድር አሰባሰብ ላይ የታየዉ ዉጤት የሚበረታታ ነው።የቋሚ ኮሚቴ አባላት ትኩረት ቢደረጉባቸው ያሏዋቸዉን ሀሳቦች በተለይ ባንኩ ያጋጠሙትን ችግሮች ለይቶ ደረጃ በደረጃ መፍታት፣ጉድለቶችን ከስር ከስር እያረሙና እያስተካከሉ መሄድ፣ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ የታገዙ ማድረግ፣አንዳንድ የስራ ክፍሎችን ለባንኩ ስራ በሚያግዝ መልኩ ማደራጀት ይገባል ብለዋል።የኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ልማት ባንክን ስራዎች በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተዘዋውረው በተግባር ባንኩ እየሰጠ ያለውን አገልግሎት መመልከታቸውንና ባዩት ነገር መደሰታቸውንም ሪፖርቱ በቀረበበት ወቅት ገልፀዋል።