የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ካለፉት ዓመታት የተሻለ ውጤት ማስመዝገቡ ተገለጸ

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በተገባደደው የ2016 በጀት ዓመት በዋና ዋና የፋይናንስ መለኪያዎች ካለፉት ዓመታት የተሻለ ውጤት ማስመዝገቡ ተገለጸ፡፡ የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ፣ የማኔጅመንት አባላት፣ እና ሰራተኞች በተገኙበት የበጀት ዓመቱ አፈጻጸም የተገመገመ ሲሆን፣ የቀጣይ ዓመት
ዕቅድም ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ክቡር አቶ ተክለወልድ አጥናፉ የሀገር ኢኮኖሚ ዋና የልማት አጋዥ እንዲሆን ታቅዶ የተቋቋመው ባንክ ለግለሰቦች መጠቀሚያ ሆኖ እንደነበር አስታውሰው በአሁኑ ሰዓት ግን የተቋቋመበትን ዓላማ መፈጸም የሚያስችል ትክክለኛ መስመር ላይ መሆኑን አንስተዋል፡፡ ለዚህም የባንኩ ማኔጅመንትና መላው ሰራተኛ የበለጠ ውጤት ለማምጣት አሁን ካለው የስራ ትጋት በተሻለ መንቀሳቀስ እና ያለበትን ትክክለኛ መስመር አስጠብቆ መቀጠል እንደሚገባ የቦርድ ሰብሳቢው አሳስበዋል፡፡