ባንኩ ለባቡል ኸይር የበጎ አድራጎት ድርጅት ድጋፍ አደረገ

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሚያዝያ 2 ቀን 2016 ዓ.ም የተከበረውን 1445ኛውን የኢድ አልፈጥር በዓልን ምክንያት በማድረግ ለባቡል ኸይር የበጎ አድራጎት ድርጅት ድጋፍ አደረገ፡፡ ባንኩ ድጋፉን ያደረገው በዓሉን በማስመልከት በሃያት ሬጀንሲ ሆቴል ባዘጋጀው ልዩ የበዓል መርሐ ግብር ሲሆን፣ የባንኩ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዮሐንስ አያሌው በተገኙበት ለድርጅቱ የ5,000,000 (አምስት ሚሊዮን) ብር የገንዘብ ድጋፍ ተደርጓል፡፡
ባቡል ኸይር የበጎ አድራጎት ድርጅት በ2012 ዓ.ም መስከረም ወር ላይ በ16 በጎ ፈቃደኛ ሴቶች ተቋቁሞ ለአምስት ዓመታት የሠራ ሲሆን፣ አሁን ላይ
4000 በላይ አባወራና እማወራ አቅመ ደካሞች ከ15 ሺሕ ልጆቻቸው ጋር በየቀኑ ይመግባል፡ ፡ 150 ተቀጣሪ ሠራተኞች ያሉት ባቡል ኸይር የበጎ አድራጎት ድርጅት ብዙዎች በበጎ ፈቃድም ያገለግሉበታል፡፡ ጓደኞቻቸውን እና ቤተሰባቸውን አስተባብረው ድርጅቱን የመሠረቱት
ወ/ሮ ሀናን ማህሙድ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለድርጅቱ የሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ በቼክ ከተቀበሉ በኋላ በሰጡት አስተያየት ‹‹የኢትዮጵያ
ልማት ባንክን በሀገርና በድርጅታችን ስም እናመሰግናለን፤ የባንኩ ማኔጅመንት በቀጣይም የበጎ አድራጎት ድርጅታችንን ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶች
እንዲጎበኝ እጋብዛለሁ›› ብለዋል፡፡ የበጎ አድራጎት ድርጅቱን ምስጉን ተግባር የተረዳው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለግንባታ የሚሆን 5000 ካሬ ሜትር ቦታ ለድርጅቱ ማስረከቡ የተገለጸ ሲሆን፣ 2.4 ቢሊዮን ብር ለሚፈጀው ለዚህ ግንባታ ድርጅቱ የኢትዮጵያ ልማት ባንክንም ድጋፍ ጠይቋል፡፡
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለአራት ችግረኛ ግለሰቦች የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል፡፡ የመጀመሪያው ‹‹ዓይነ ስውሩ ቴክኒሻን›› ሸክ መሐመድ ኑር ከሊፋ ሲሆኑ ማየት የተሳናቸው ሆነው ሳለ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎችን ጥንቅቅ አድርገው የሚጠግኑ ባለሙያ ናቸው፡፡ ኑሯቸውን በአዋሬ አድርገው
በርካታ ዓመታትን አሳልፈዋል፡፡ እኚህ የቴክኒክ ባለሙያ በቂ የመሥሪያ ቦታ ስለሌላቸውና ሥራቸውን በዘመናዊ መልክ ለማደራጀት እንዲረዳቸው
እንዲሁም የሥራን ክቡርነት ላሳዩበት እንደማበረታቻ የ600,000 / ስድስት መቶ ሺህ ብር ድጋፍ ተደርጎላቸዋል፡፡