የ50ኛ ዓመት የጋብቻ የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓልን ምክንያት በማድረግ የቦንድ ግዥ ተፈጸመ
ታዋቂው የፋይናንስ ባለሙያ አቶ ኢየሱስወርቅ ዛፉ እና ባለቤታቸው የ50ኛ ዓመት የጋብቻ የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓላቸውን ምክንያት በማድረግ በባንኩ ዋናው መ/ቤት በአካል በመገኘት ከወለድ ነጻ የሆነ የአንድ ሚሊዮን ብር የቦንድ ግዥ ፈጽመዋል፡፡
በተያያዘም ኢንጂነር ተረፈ ራስወርቅ የዛሬ ስምንት ዓመት የ50ኛ ዓመት የጋብቻ የወርቅ ኢዮቤልዩን በማስመልከት በልጅ እና ልጅ ልጆቻቸው ሥም ለእያንዳንዳቸው የ50 ሺህ ብር የቦንድ ግዥ ፈጽመው የነበሩ ሲሆን አሁንም በልጃቸው ሥም የብር 350 ሺህ የቦንድ ግዥ ፈጽመዋል፤ በአጠቃላይ ቤተሰቡ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ግዥ አከናውነዋል፡፡
በቦንድ ግዥ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ኃይለየሱስ በቀለ የህዳሴ ግድቡ ሙሌት ሥራ መጀመሩ ትልቅ ብሥራት መሆኑንና ለዚህም ባንኩ ከመጀመሪያው ጀምሮ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም በቅርቡ ለግድቡ ግንባታ የብር 5 ሚሊዮን ቦንድ ገዝቶ በስጦታ መለገሱን፣ ከሥራ መሪዎች ጀምሮ ከደመወዛቸው ላይ እያዋጡ እንደሚገኙ እና የግድቡ ግንባታ ሥራ ስላልተጠናቀቀ ለወደፊቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አብራርተዋል፡፡ በዚሁ ዓላማ አንጋፋዎቹ ሰዎች ባንኩ ድረስ በመምጣት የቦንድ ግዥውን በመፈጸማቸው ፕሬዚዳንቱ ከፍ ያለ ምሥጋና አቅርበዋል፡፡
አቶ ኢየሱስወርቅ ዛፉ የህዳሴ ጉዳይ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አስተዋጽዖ ያለበትና “አሻፈረኝ እምቢ የምትል ኢትዮጵያ ተፈጥራለች” በማለት የገለጹ ሲሆን ኢንጂነር ተረፈ ራስወርቅ በበኩላቸው “ግድቡ የእኛ ነው” የሚለው አባባል ትልቅ መልእክት ያዘለና ሁላችንንም የሚያስተሳስረን ነው ብለዋል፡፡
ሕጻናት ለልደታቸው በተቀመጠው ብር የቦንድ ግዥ ፈጸሙ
የአቶ በኃይሉ ዳንኤል ሶስት ህጻናት ልጆች እና ባለቤታቸው ልደታቸውን ለማክበር የተቀመጠላቸውን ብር ለቦንድ ግዥ አውለዋል፡፡ ግዥውን የፈጸሙት ሐምሌ 08 ቀን 2012 ዓ.ም በኢትዮጵያ ልማት ባንክ ዋናው መ/ቤት በመገኘት ነው፡፡
በእለቱ የባንኩ ተ/ም/ፕሬዚዳንት ኮርፖሬት አገልግሎት አቶ ደሳለኝ ቦጋለ ይህ ተግባር ለሌሎች መሰል የነገ አገር ተረካቢ ህጻናት እና መላው ህብረተሰብ አርአያ የሚሆን ስለሆነ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል በማለት አበረታተዋል፡፡
በመቀጠል ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽ/ቤት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ኃይሉ አብርሐም በበኩላቸው መንግስት ህብረተሰቡን በማስተባበር ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ግንባታውን እየፈጸመና የውሃ ሙሌቱንም እንደጀመረ ተናግረው ሌሎችም ይህን አርአያነት ያለው ተግባር በመከተል ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ቦንድ እንዲገዙ እና ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የሕጻናቱ አባት ሶስቱ ልጆቻቸው እና ባለቤታቸው ልደታቸውን ለማክበር ለእያንዳንዳቸው በተቀመጠው ብር አምስት ሺህ በድምሩ የብር 20 ሺህ ብር ቦንድ በራሳቸው ተነሳሽነት ገዝተዋል በማለት ገልጸዋል፡፡
በባንኩና በባንኩ ሠራተኛ ማህበር መካከል የሕብረት ስምምነት ፊርማ ሥነ ሥርዓት ተካሄደ
በኢትዮጵያ ልማት ባንክ እና በባንኩ ሠራተኛ ማህበር መካከል ለ12ኛ ጊዜ የሕብረት ስምምነት ፊርማ ሥነ ሥርዓት ተካሄደ፡፡ የፊርማ ሥነ ሥርዓቱ የተካሄደው ሐምሌ 09 ቀን 2012 ዓ.ም በኢንተርኮንቲነንታል ሆቴል ነው፡፡
በሥነ ሥርዓቱ ላይ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ኃይለየሱስ በቀለ፣ ምክትል ፕሬዚዳንቶች፣ የባንኩ ሠራተኛ ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉቀን አመነ እና ሥራ አስፈጻሚዎች፣ የባንክና መድን ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ደስታ በርሔ ተገኝተዋል፡፡
የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ኃይለየሱስ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት ባንኩ ከሠራተኛ ማህበሩ ጋር በቅርበት ተሳስቦ እየሠራ እንደሚገኝ እና ይህ ተግባር ለወደፊቱም በተሻለ ሁኔታ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡ በተያያዘም በህብረት ስምምነቱ ላይ ለተሳተፉት አካላት በሙሉ ምሥጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የማህበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉቀን አመነ በበኩላቸው ማህበሩ የሠራተኛውን ጥቅማጥቅም ለማስከበር ከባንኩ ማኔጅመንት ጋር በውይይት እየሠራ የሚገኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ደስታ በርሔ በበኩላቸው የባንኩ ማኔጅመንት እና ሠራተኛ ማህበሩ በመነጋገርና በመወያየት ከአቻ ባንኮች ጋር ተመሳሳይ ጥቅማጥቅሞች እንዲከበሩ ለሚያደርጉት ጥረት በሙሉ ፌዴሬሽኑ አድናቆቱን ገልጾ ፌዴሬሽኑ ለወደፊቱ እገዛውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አብራርተዋል፡፡
በህብረት ስምምነቱ ውስጥ አዲስ የገቡ እና የተሻሻሉ አንቀጾችና ንዑስ አንቀፆች ተካትተዋል፤ ከእነዚህ መካከል የሠራተኛ ቅጥር፣ ዝውውር፣ ደመወዝና ልዩ ማበረታቻ፣ የወሊድ ፈቃድ፣ የአባትነት ፈቃድ፣ ለሠራተኛ የሚሰጥ ብድር፣ ስለደረጃ ዕድገት፣ ትምህርትና ሥልጠና፣ የሕዝብ በዓላት፣ የትርፍ ሰዓት ሥራና ክፍያ፣ የቀን ውሎ አበል፣ የሐዘን ፈቃድ፣ ከሥራ ጋር ግንኙነት ስላለው በሽታና የአካል ጉዳት፣ በባንኩ የሚሸፈኑ የሕክምና ወጪዎች፣ የዲስፕሊን እርምጃ እንዲሁም ስለ ደንብ ልብስና የአደጋ መከላከያ ዘዴዎች ናቸው፡፡
ባንኩ ለሚዲያ አካላት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጠ
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሰኔ 04 ቀን 2012 ዓ.ም. ለሚዲያ አካላት በኮቪድ-19 እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ በኢንተርኮንቲነንታል ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ኃይለየሱስ በቀለ በአሁኑ ጊዜ በዓለምአቀፍም ሆነ በሀገራችን በተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በባንኩ ብድር የተቋቋሙ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ላይ የራሱን አሉታዊ ተጽእኖ ማሳደሩን ገልጸው ባንኩም የራሱን የፕሮጀክት ማገገሚያ ስልቶችን በማዘጋጀት እና ጤናማ የሆኑ ፕሮጀክቶች በመለየት፣ በባንኩ ሥራ አስፈጻሚ እና ሥራ አመራር ቦርድ ታይተው ተገቢው ድጋፍ እንዲደረግላቸው እና የልዩ ልዩ ማሻሻያዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ውሳኔዎች መተላለፋቸውን ተናግረዋል፡፡
በተቋም ደረጃም የባንኩን ሠራተኞች እና ደንበኞች ከወረርሽኙ ለመከላከል የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች መሠራታቸውን፣ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች (ሳኒታይዘር እና አልኮል) መከፋፈላቸውን፤ በሥራ ቦታ አካላዊ ርቀት ተጠብቆ እንዲሠራ መደረጉን፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎች መታደላቸውን እና በሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓት የትራንስፖርት አገልግሎት መመቻቸቱን ገልጸዋል፡፡
ኮቪድ-19 የሚያደርሰውን ወረርሽኝ ለመከላከል እንዲቻል በሀገር አቀፍ ደረጃ ለተቋቋመው የኮቪድ-19 ግብረ ኃይል እንዲሁ የአምስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን የባንኩ ፕሬዚዳንት ተናግረዋል፡፡
የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት (MFIs) እና የኅብረት ሥራ ማኅበራት ባጋጠማቸው የገንዘብ እጥረት እና የእነሱ ተጠቃሚ ለሆኑ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ደንበኞቻቸው በአነስተኛ ወለድ የብድር አቅርቦት እንዲስተናገዱ መደረጉን አቶ ኃይለየሱስ ጨምረው አብራርተዋል፡፡
በመጨረሻም ከእርሻ ብድሮች ጋር በተያያዘ እንዲሁም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በባንኩ ገቢ ላይ ስላስከተለው ጉዳት እና በቀጣይ ምን ለመሥራት እንደታሰበ ከሚዲያ ባለሙያዎች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
Page 24 of 31