የኢትዮጵያ ልማት ባንክ እና የብሄራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት አብሮ ለመስራት የሚያስችላቸውን ውይይት አደረጉ

 

የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ትግስቱ አምሳሉ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ በመሆኑ ከብሄራዊ የእስሳት ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በትብብር ለመስራት የሚያስችለውን ውይይት ማድረጉ ሀገሪቱ ከዘርፉ የምታገኘውን ገቢ በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ እንደሚረዳው ገልፀዋል።

በውይይት መድረኩ የተገኙት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዮሐንስ አያሌው ባንኩ የፖሊሲ ባንክ እንደመሆኑና ሀገራችን ቅድሚያ ሰጥታ ለማልማት ከምትሰራባቸው ዘርፎች መካከል አንዱ የሆነውን የእንስሳት ሀብት በአግባቡ፣ጤንነቱን በጠበቀና በዘመናዊ መንገድ ለመጠቀም የብሄራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት እያደረገ ያለው አስተዋፆ የላቀ በመሆኑ በጋራ መስራታቸው ወሳኝ መሆኑን ነው ያስገነዘቡት።

የኢንስቲትዩቱን አጠቃላይ የስራ እንቅስቃሴ ተዘዋውረው መጎብኘታቸው ኢትዮጵያ ከቫይረስና ከባክቴሪያ የሚመጡ የእንስሳት በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ የተለያዩ የእንስሳት ክትባቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ለሀገር ውስጥ ገበያ እያቀረበ የሚገኝ ሁነኛ የሀገር ሀብት እንዳላት የተገነዘቡበት መሆኑንም ነው ያስታወቁት።

ዶ/ር ዮሃንስ አያሌዉ እንዳሉት ባንኩ ቅድሚያ ከሚሰጠዉ አንዱ የእንሰሳት ዘርፍ እንደመሆኑ ለተያዙት ፕሮጀክቶች የአዋጭነት ጥናት /feasibility study ኢንስቲትዩቱ ለባንኩ እንዲያቀርብና በጥናቱ መሰረት እገዛ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ አክለውም ይህን የሀገር ሀብት ወደ ላቀ ደረጃ መጠቀም እና ማምረት እንዲያስችል በጋራ መስራታቸው ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም ነው ያሉት።

 የኢንስቲትዩቱ የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር በሬቻ ባይሳ የምርምር ስራዎችን ፣የክትባት ማምረቻ ላብራቶሪዎች ያሉበትን ደረጃ፣የመድሃኒት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ በተመለከተ እንዲሁም የአገር ውስጥ የእንስሳት ክትባት ፍላጎትን ሙሉ ለሙሉ በመሸፈን ለክትባት ግዢ ይወጣ የነበረን የውጭ ምንዛሪ ማስቀረቱንም  ነው በማብራሪያቸው የገለፁት፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የኮርፖሬት ግብርና ዘርፍ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ዋቄ በበኩላቸው ባንኩ በልዩ ትኩረት ግብርናውን ለማዘመን እየሰራ በመሆኑና በርካታ በዘርፉ የሚሰማሩ ኢንቨስተሮች ወደ ባንኩ እየመጡ በመሆናቸው ለእንስሳት ጤና የሚሆነውን ክትባት በቅርበት እንዲያገኙ እና የዘርፉን ቢዝነስ ለማሳደግ ከኢንስቲትቱ ጋር መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ብሄራዊ የእስስሳት ጤና ኢንስቲትዩት በአሁኑ ጊዜ 23 ዓይነት የእንስሳት በሽታ መከላከያ ክትባቶችን እያመረተ ይገኛል፡፡ በዚህም የሚያመርታቸውን ክትባቶች ወደ ጎረቤትና ሌሎች የአፍሪካ አገራት በመላክ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ማግኘት መቻሉን፤እንዲሁም በቀጣይ የእንሰሳት መኖ ማቀነባበሪያ ፣ተቋሙ ሲመሰረት የተገነቡ ላብራቶሪዎችን በዘመናዊ የአመራረት ዘዴ /GMP የመቀየር፣የእንስሳት መመርመሪያ ኪት ለማምረት፣መድሃኒቶችን ከእንክብል በመርፌ ወደሚሰጥ ለማዘጋጀት በእቅድ ላይ እንደሆነና እነዚህን ወደ ተግባር ለመለወጥ የታሰቡ ፕሮጀክቶችን ወደ ተግባር በመቀየር በኩል የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የፋይናንስ የብድር ስርዓቱን ተከትሎ እንዲያግዘው የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ታከለ አባይነህ ጠይቀዋል፡፡

ዋና ዳይሬከተሩ አክለውም ኢንስቲትዩቱ በእንስሳት ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ድጋፍ የሚያደርግ ተቋም እንደመሆኑ ስትራቴጂ ተነድፎ የገበያ ዕድል ከመፍጠር አንጻርና ፕሮጀክቶቹን ተግባራዊ ለማድረግ ሙሉ አቅሙን በመጠቀም የአዋጭነት ጥናት ለኢትዮጵያ ልማት ባንክ ያቀርባል ብለዋል፡፡

የብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት ከተመሰረተ ከ60 ዓመታ በላይ ብቸኛ በእንስሳት ጤና ላይ የሚሰራ የልማት ድርጅት ሲሆን፤ በአሁን ወቅት በዓመት ከ350 ሚሊዮን ዶዝ በላይ ክትባት እያመረተ ይገኛል፡፡