የኢትዮጵያ ልማት ባንክ 20 ሚሊዮን ብር ለበጎ አድራጎት ስራ ድጋፍ አደረገ

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለመቄዶኒያ የአረጋውያንና የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል እንዲሁም ለዲቦራህ ፋውንዴሽን ሰኔ 29 ቀን 2014 .ም የ20 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ አደረገ፡፡

ባንኩ በመንግስት ትኩረት ለተሰጡ የልማት ፕሮጀክቶች ብድር ከመስጠት ባሻገር ማህበራዊ ኃላፊነቱን ይበልጥ ለመወጣት ለመቄዶኒያ የአረጋውያንና የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል 15 ሚሊዮን ብር፣ እንዲሁም ለዲቦራ ፋውንዴሽን ደግሞ የ5 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዮሐንስ አያሌው ከባንኩ የማኔጅመንት አባላት ጋር በበጎ አድራጎት ተቋማቱ በአካል በመገኘት ድጋፉን አበርክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት፣ ዶ/ር ዮሐንስ አያሌው ድጋፉን በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት ባንኩ ከመቄዶኒያ የአረጋውያንና የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ጋር በቅርበት እየሰራ ሲሆን፣ በተለያዩ ወቅቶችም የተለያየ መጠን ያለው የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ማዕከሉ ለባንኩ ባደረገው የድጋፍና የጉብኝት ጥሪ መሰረት በከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን አይዧችሁ ለማለትና የዘወትር አጋርነቱን ለመግለጽ የገንዘብ ድጋፉ እንደተደረገም ገልጸዋል፡፡

ዶ/ር ዮሐንስ አያሌው የበጎ አድራጎት ድርጅቱ አስተዋጽኦ ያላቸውን አድናቆት ገልፀው በቀጣይነትም የተለያዩ ድጋፎችን ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡

የአረጋውያንና የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከሉ መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ፣ ክቡር ዶ/ር ቢኒያም በለጠ በበኩላቸው ማዕከሉ በአሁኑ ጊዜ ከ7500 በላይ የሆኑ አረጋዊያን፣ የአእምሮ ህሙማን እና በተለያዩ ምክንያቶች ችግር ላይ የወደቁ ዜጎችን ከወደቁበት በማንሳት እየተንከባከባቸው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

 

ባንኩ በተለያዩ ምክንያቶች ከፍተኛ ችግር ላይ ወድቀው በማዕከሉ እየተደረዱ ለሚገኙ ወገኖች ያለማቋረጥ እያደረገ ያለውን ድጋፍ በማመስገን ለወደፊቱም ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

በማዕከሉ ድጋፍ እየተደረገላቸው የሚገኙ የአረጋዊያን ተወካዮችም በበኩላቸው ባንኩ እያደረገ ለሚገኘው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ በዕለቱ ባንኩ የ5 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ ለዲቦራ ፋውንዴሽን ያበረከተ ሲሆን፤ የተከበሩ አቶ አባዱላ ገመዳ፣ የዲቦራ ፋውንዴሽን መስራችና የቦርድ ሊቀመንበር የ5 ሚሊዮን ብር ቼክ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዮሐንስ አያሌው እጅ ተረክበዋል፡፡

በቼክ ርክክብ ሥነ ስርዓቱ ላይ ዶ/ር ዮሐንስ አያሌው የአእምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው ህጻናትና ወጣቶችን በመደገፍ በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ንቁ ተሳታፊዎች እንዲሆኑ እንደ ልማት ባንክ ካሉ የፋይናንስ ተቋማትና፣ በአጠቃላይ ድጋፍ ማድረግ ከሚችሉ ሁሉ የሚጠበቅ ተግባር መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ለፋውንዴሽኑ የሚደረግ የገንዘብ ድጋፍም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የዲቦራ ፋውንዴሽን መስራችና የቦርድ ሊቀመንበር የተከበሩ አቶ አባዱላ ገመዳ በበኩላቸው ፋውንዴሽኑ ከ1,500 በላይ የአእምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው ህጻናትን እየተንከባከበ እንደሚገኝ የገለጹ ሲሆን፤ ስራውንም በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች በማስፋፋት ችግሩ ያለባቸውን ህጻናት ለመደገፍ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡