በሥልጠና ለተሳተፉ አስተባባሪዎች የምስጋና መርሐ ግብር ተካሔደ

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በሦስተኛው ዙር ሀገር አቀፍ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች ሥልጠና በአስተባባሪነት የተሳተፉ ሠራተኞቹን ያመሰገነበትን መርሐ ግብር አርብ፣ ግንቦት 27 ቀን 2014 ዓ.ም በባንኩ ስብሰባ አዳራሽ አካሒዷል፡፡

ከግንቦት 5 እስከ ግንቦት 27 ቀን 2014 ድረስ ባሉ ቀናት በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች የተካሔደውን ሥልጠና በዐቢይና ንዑሳን ኮሚቴዎች ተደራጅተው ላስተባበሩ የባንኩ ሠራተኞችና ሥራ ኃላፊዎች የባንኩ ፕሬዚዳንት ክቡር ዮሐንስ አያሌው/ፒኤ.ች.ዲ/ በተገኙበት የምስጋናና እውቅና መርሐ ግብሩ ተካሂዷል፡፡ 

የባንኩ ፕሬዚዳንት በመድረኩ ተገኝተው ለአስተባባሪዎች የምስክር ወረቀት በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት በዐቢይ ኮሚቴው ጥብቅ ክትትል በየማእከላቱ በሚገኙት ኮሚቴዎች መነቃቃትና ትጋት በሚፈለገው ደረጃ ሥልጠናው መመራቱ ስኬታማና ውጤታማ እንዲሆን አስችሎታል ብለዋል፡፡ ለዚህም በሁሉም ደረጃ ለነበሩ አስተባባሪዎች እና ሠራተኞች ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

የባንኩ ፕሬዚዳንት አክለው በዚህ ደረጃ ያለን ግዙፍ ሀገር አቀፍ ሥልጠና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን በመጠቀም ባንኩ ልምድ ሊቀሰምበት የሚገባ ታሪካዊ አፈጻጸም አስመዝግቧል ብለዋል፡፡ በ20 ከተሞች በተካሔደው በዚህ ሥልጠና ከ27 ሺህ በላይ ሠልጣኞች መሳተፋቸው ይታወሳል፡፡