‘’የዲጂታል ቴክኖሎጂ አቅም መገንባት አማራጭ ሳይሆን ግዴታ ነው’’ ፡- /ር ዮሐንስ አያሌው የኢልባ ፕሬዚዳንት

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15 2014 (ኢልባ)  የኢንፎርሜሽን ዲጂታል ሥርዓት የሀገራት መወዳደሪያ ጡንቻ በሆነበት በዚህ ወሳኝ ወቅት የተቋማት መረጃን ከማንኛውም ዓይነት የሳይበር ጥቃት መጠበቅ ትኩረት የሚሻ መሆኑን የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚደንት ዶ/ር ዮሐንስ አያሌው ተናግረዋል፡፡

ፕሬዚደንቱ ይህንን ያሉት ዛሬ ለባንኩ የሥራ አመራር አባላት በሳይበር ደኅንነት ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና በተሰጠበት ወቅት ነው፡፡

የሳይበር ጥቃትን ለመከላከል እና የተቋማትን መረጃ አደራጅቶ ለመያዝ ደግሞ ራሱን የቻለ እውቀትና ክህሎት የሚጠይቅ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ዶ/ር ዮሐንስ ገልጸዋል፡፡

ሀገራት ሉዓላዊነታቸውንና አጠቃላይ ህልውናቸውን አረጋግጠው ለመኖር የዲጂታል ቴክኖሎጂ አቅምን መገንባት አማራጭ ሳይሆን ግዴታ የሆነበት ዘመን ላይ እንገኛለን ሲሉም አክለዋል፡፡

ከዚህ አንጻር የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ሥልጠናውን ለመስጠት ላሳየው ተነሣሽነት ምስጋናቸውንም አቅርበዋል፡፡

በሥልጠናው የተገኙት የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሹመቴ ግዛው በበኩላቸው ለሳይበር ደኅንነት ጥቃት ትኩረት ባለመሰጠቱ በርካታ ጉዳቶች እየደረሱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 

የሳይበር ጥቃት ደኅንነትን መጠበቅና ማስጠበቅን ለማረጋገጥ ሦስት መሠረታዊ ነገሮችን ማሟላት ይጠይቃል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ፤ እነዚህም እውቀትና ክህሎት ያለው የሰው ኃይል፣ በአግባቡ መሥራት የሚችል ተወዳዳሪ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችና ትክክለኛ የአሠራር ሥርዓት መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ይህ ሲሟላም የሳይበር ደኅንነት አስተማማኝ ደረጃ ላይ ይደርሳል ብለዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ ለወደፊቱ ተመሳሳይ ሥልጠና ለባንኩ አመራሮችና ሠራተኞች ለመስጠት ተቋማቸው ፈቃደኛ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡