ስድስተኛው ዙር የቦንድ ሳምንት ተጀመረ

 

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 20 2014 (የኢትዮጵያ ልማት ባንክ)

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ስድስተኛው ዙር የቦንድ ሽያጭ ሳምንት ትናንት በኢሊሌ ሆቴል በተዘጋጀ ሥነ ሥርዓት ተጀመረ፡፡

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ 11ኛ ዓመትን አስመልክቶ የተዘጋጀውን ስድስተኛውን ዙር የቦንድ ሳምንት፤ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የግድቡ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት በጋራ አዘጋጅተዋል፡፡ የቦንድ ሳምንቱ ለ15 ቀናት የሚቆይ ነው፡፡

በዚሁ ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ላይ የኃይል ማመንጨት ሥራውን በስኬት የጀመረው የሕዳሴው ግድብ ሙሉ ግንባታውን ከፍጻሜ ለማድረስ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ቦንድ በመግዛት የሚያደርገውን ተሳትፎ እንዲያጠናክር የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ቦንድ ሳምንቱ ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት የብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶ/ር ይናገር ደሴ፣ ግድቡ በሙሉ አቅሙ ኃይል ለማመንጨት እና ለመጠናቀቅ ከሦስት ዓመታት ያነሱ ጊዜያት ብቻ ስለቀሩት በርብርብ ማጠናቀቅ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ግድቡ ከብዙ ዓመታት ውጣ ውረድ በኋላ ኃይል ማመንጨት ጀመረ እንጂ አልተጠናቀቀም ያሉት ዶ/ር ይናገር፤ ግድቡን ለማጠናቀቅ ተጨማሪ ገቢ ማሰባሰብ ስለሚገባ በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቦንድ በመግዛት የጀመሩትን ግድብ እንዲጨርሱ አደራ ብለዋል፡፡

የኃይል ማመንጫ ግድቡ ሲጠናቀቅ ለኢትዮጵያ ልማት አዲስ ምዕራፍ እንደሚከፍት ጠቁመው ብሔራዊ ባንክም በቦንድ ማከፋፈልና ሽያጭ ላይ ለተሰማሩ የፋይናንስ ተቋማት እገዛ እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የኮርፖሬት አገልግሎት ምክትል ፕሬዝደንት አቶ ሰፊዓለም ሊበን በበኩላቸው ባንኩ ባሳለፍነው የካቲት ወር መጨረሻ ድረስ 24 ቢሊዮን ብር የሚደርስ ቦንድ ማሳተሙን አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በ11 ዓመታት ውስጥ የ14 ቢሊዮን ብር የቦንድ ሽያጭ አከናውኑም ነው በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት የተብራራው፡፡

ሁሉም ትዮጵያዊ የአቅሙን በማበርከቱ ግድቡ አሁን ላይ የ84 በመቶ አፈጻጸም እንዲኖረው ማስቻሉን የተናገሩት ምክትል ፕሬዝደንቱ ቀሪውን የግድቡን ግንባታ ከፍጻሜ ለማድረስ የሕዝቡ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንዲጠናከር ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ግድቡ እስካሁን ድረስ የሕዝብና የተቋማት ድጋፍ አልተለየውም ያሉት አቶ ሰፊዓለም፤ በተጀመረው የቦንድ ሽያጭ ሳምንት ሁሉም ኢትዮጵያውያን እንዲሳተፉና የአቅማቸውን ያክል ቦንድ እንዲገዙ አደራ ብለዋል፡፡

ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ታገል ቀኑብህ እንዳሉት ግድቡ በአሁኑ ስዓት 375 ሜጋ ዋት ኃይል እያመነጨ ይገኛል፡፡

ለግድቡ ግንባታም ባለፉት 11 ዓመታት ኢትዮጵያውያን 16 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በቦንድ እና በስጦታ ማበርከታቸውን ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡

በርካታ ኢትዮጵያውያን በሙያቸው እና በእውቀታቸው ድጋፍ ማበርከታቸውን ያስታወቁት አቶ ታገል አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ጉልበቱን በተፋሰስ ሥራ ላይ በማዋል የበኩሉን ድርሻ ተወጥቷል፡፡

በመጪው መጋቢት 24 የሚከበረው የግድቡ ግንባታ 11ኛ ዓመት ‘’ግድባችን የአንድነታችን ብርሃን’’ በሚል መሪ ሀሳብ እንደሚከበር ከሕዝባዊ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በቦንድ ሳምንቱ ተገኝቶ ቦንድ ሲገዛ ያገኘነው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ዮሐንስ ፍስሓ ግድቡን በተመለከተ ቦታው ድረስ በመሄድ 12 ጊዜ መዘገቡን ይናገራል፡፡

ግድቡ ያጋጠሙትን ፈተናዎችና የደረሰበትን ስኬት ስዘግብ ቆይቻለው ፤ አሁን ደግሞ ለፍጻሜ እንዲበቃ ቦንድ በመግዛት የድርሻዬን እየተወጣሁ ነው ብሏል፡፡

ከመጋቢት 20 እስከ ሚያዚያ 5 ቀን 2014 .ም በሚቆየው የቦንድ ሽያጭ ሳምንት ከመቶ ብር ጀምሮ የተለያየ ዋጋ ያላቸው ቦንዶች ለሽያጭ ቀርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በግድቡ የግንባታ ሂደት ዜጎች በቦንድ ግዥ ሰፊ ተሳትፎ እንዲያደርጉ እና ተጨማሪ ድጋፎችን በማበርከት ግድቡ አሁን ለደረሰበት ደረጃ ቁልፍ ሚና እየተወጣ ያለ ባንክ መሆኑም በመግለጫው ተመላክቷል፡፡