ባንኩ ስፖንሰር ያደረገው ከወለድ ነጻ የባንክ እና የኢንሹራንስ አገልግሎት መድረክ ተካሄደ

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በዋና አጋርነት ስፖንሰር በማድረግ የተሳተፈበት ከወለድ ነጻ የባንክ እና የኢንሹራንስ አገልግሎት ላይ ያተኮረ መድረክ መጋቢት 7 ቀን 2014 ዓ.ም በሸራተን አዲስ ተካሂዷል፡፡

 

 

በመድረኩ ላይ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የኢትዮጵያ የአካውንቲንግ እና ኦዲቲንግ ቦርድ ዳይሬክተር ጄኔራል፣ የግል ባንክ እና ኢንሹራንስ ተወካዎች፣ ባለድርሻ አካላት እና አማካሪ ድርጅቶች ተገኝተዋል፡፡

ባንኩን በመወከል መድረኩ ላይ የተገኙት ም/ፕሬዚዳንት- ኮርፖሬት አገልግሎት አቶ ሰፊዓለም ሊበን መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ በመልእክታቸው የኢትዮዽያ ልማት ባንክ የሸሪአ መርሆዎችን የተከተለ ከወለድ ነጻ የሆነ የትላልቅ ፕሮጀክትና የሊዝ የፋይናንስ አገልግሎት ለመስጠት ተገቢውን ጥናት አስጠንቶ አገልግሎቱን ባስቀመጣቸው ስትራቴጂዎች በቅርቡ እውን ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን በማጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

 

ባንኩ በሌሎች ባንኮች ሊሸፈኑ የማይችሉ የፋይናንስ አገልግሎቶችን በማቅረብና የሀገሪቱን የማክሮ ኢኮኖሚ ክፍተት በመሙላት በሀገራዊ እድገት ላይ የራሱን ሚና በመጫወት እንደሚገኝ በመግለጽ አገልግሎቱን ከሚሹ ሁሉም ደንበኞቹ ጋር በጋራ ለመስራት ባለው ጠንካራ ፍላጎት የተነሳ የረጅም ጊዜ ብድር ወስደው በልማት ስራ ላይ በማዋል ራሳቸውንና ሀገራቸውን እንዲያሳድጉ  ም/ፕሬዚዳንቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በቀጣይነትም ባንኩ ሀገራዊ እድገት ላይ አስተዋጽኦ ያላቸውን የግንዛቤ መፍጠሪያ መሰል መድረኮችን ለመደገፍ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አክለዋል፡፡